የሩሲያ ጦር በምስራቃዊ ዩክሬይን ተጨማሪ ከተሞችን ለመያዝ ጥቃት መክፈቱን የዩክሬይን ሹሞች ተናገሩ፡፡
የሰሜን ምስራቋ ከተማ ሐርኪቭ በሩሲያ ሀይሎች እየተመታች መሆኑን ሲድኒ ሞርኒንግ ሔራልድ ፅፏል፡፡
ኒኮፖል የተባለችው ከተማም የሩሲያ ጦር የጥቃት ዒላማ ነች ተብሏል፡፡
ከተማዋ የዩክሬይን ከፍተኛው የኒኩሊየር የኤሌክትሪክ ማመንጫ የሚገኝባት እንደሆነች ዘገባው አስታውሷል፡፡
የሩሲያ ጦር በደቡብ የአገሪቱ ክፍል የሚገኘውን የዛፖሮዢያን የኒኩሊየር የኤሌክትሪክ ማመንጫ የተቆጣተረው በጦርነቱ መጀመሪያ ወቅት ነው፡፡
የሩሲያ ጦርቀጣዩ ትኩረት የሐርኪቭ ከተማ እንደሆነች ይነገራል፡፡
ስለ ሐርኪቩ ጥቃት ከሩሲያ በኩል የተሰማ አስተያየት የለም፡፡
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር አብዱላሂያን እስራኤል በጋዛ ትፈፅመዋለች ያሉትን የዘር ፍጅት እና የጦር ወንጀል በአስቸኳይ ካላቆመች ድፍን ቀጠናው ወደማያባራ ትርምስ ያመራል ሲሉ ማስጠንቀቃቸው ተሰማ፡፡
የአብዱላሂያን መሰል ማስጠንቀቂያ የመጀመሪያ አይደለም፡፡
አዲሱን ማስጠንቀቂያ የደገሙት የደቡብ አፍሪካዋን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶርን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት እንደሆነ UPI ፅፏል፡፡
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካም ለእስራኤል የጦር መሳሪያ እና ሁለንተናዊ ድጋፍ በመስጠት ተጠያቂ ነች ብለዋል፡፡
እስራኤል በጋዛ ታደርሰዋለች ያሉት ፍጅት በአጣዳፊ ካልቆመ ቀጠናው ከቁጥጥር ውጭ ወደሆነ ትርምስ ሊያመራ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
የጋዛው ጦርነት ከ2 ሳምንታት በላይ ሆኖታል፡፡
ሰብአዊ እርዳታ የያዙ 14 የጭነት ተሽከርካሪዎች ጋዛ ሰርጥ መድረሳቸው ተሰማ፡፡
ተሽከርካሪዎቹ ጋዛ መድረሳቸውን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ እርዳታ ሹሞችም እንዳረጋገጡ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
14 የጭነት ተሽከርካሪዎች ጋዛ የደረሱት ከበርካታ ቀናት ደጅ ጥናት በኋላ መሆኑ ታውቋል፡፡
በጋዛ ከተፈናቃዮቹ ብዛት እና ከሰብአዊ ቀውሱ መግዘፍ የተነሳ በየእለቱ ቢያንስ 500 የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ሊገቡ ይገባል ሲባል ሰንብቷል፡፡
የመጀመሪያዎቹ 14 የረድኤት ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ መግባት እንደ ተስፋ ብልጭታ ተቆጥሯል፡፡
ያም ሆኖ የእስራኤሉ የአገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስቴር ቤን ግቪር ሐማስ የያዛቸውን ታጋቾች ካልለቀቀ የተጀመረው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ሊቋረጥ ይችላል ሲሉ ማስጠንቀቃቸው ተሰምቷል፡፡
ሐማስ ከ2 ሳምንታት በፊት ወደ እስራኤል በዘለቀበት አጋጣሚ ከ200 በላይ ሰዎችን አግቶ ወደ ጋዛ መውሰዱ ይነገራል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የሊባኖሱ ሔዝቦላህ ከእስራኤል ጋር ወደ ጦርነት የሚገባ ከሆነ ታላቅ ስህተት መፈፀሙን መረዳት ይኖርበታል አሉ፡፡
ኔታንያሁ የእስራኤል ጦር በአሁኑ ወቅት በሁለት ግንባሮች መሰለፉን እንደተናገሩ አናዶሉ ፅፏል፡፡
ጦሩ በደቡብ የፍልስጤማውያኑን ሐማስ እስከ ወዲያኛው ለመደምሰስ እና በሰሜን ደግሞ የሄዝቦላን ስጋትነት ለማስቆም መሰለፉን ተናግረዋል፡፡
እስራኤል ሐማስን እና ሔዝቦላህን አሸባሪዎች ስትል ትጠራዋለች፡፡
ሐማስ እና ሔዝቦላህ የኢራን ጥብቅ ወዳጆች እና አጋሮች መሆናቸው ይነገራል፡፡
ኔታንያሁ የጋዛ ዘመቻችን የሞት እና የሽረት ይሆናል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ለወራትም ሊዘልቅ እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
ሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments