የፍልስጤማዊያኑ የጦር ድርጅት /ሐማስ/ ተጨማሪ 2 ሴት ታጋቾችን መልቀቁ ተሰማ፡፡
ሐማስ ቀደም ሲል አግቷቸው ከነበሩት መካከል አንዲትን አሜሪካዊት ከነሁለት ልጆቿ የለቀቀው ሰሞኑን ነው፡፡
ሐማስ ተጨማሪዎቹን 2 ሴት ታጋቾች የለቀቅኩት በሰብአዊ ምክንያቶች መነሻ ነው ማለቱን ዩሮ ኒውስ ፅፏል፡፡
የተጨማሪዎቹን 2 ሴት ታጋቾች መለቀቅ የእስራኤሉም የመከላከያ ሚኒስትር ሞአብ ጋላንትም አረጋግጠዋል ተብሏል፡፡
ሐማስ ከ2 ሳምንታት በፊት ወደ እስራኤል በመዝለቅ ድንገት ደራሽ ጥቃት በፈፀመበት ወቅት ከ2 መቶ ያላነሱ ታጋቾችን ወደ ጋዛ ይዞ መምጣቱ ሲነገር ሰንብቷል፡፡
ከጦርነቱ ባልተናነሰ የታጋቾቹም ነገር አብይ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
በኮንጎ ኪንሻሣ በደረሰ የጀልባ ተገልብጦ መስጠም አደጋ በጥቂቱ የ28 ሰዎች ሕይወት ሳያልፍ አይቀርም ተባለ፡፡
አደጋው በኢኩዌተር ግዛት ቅዳሜ እለት የደረሰ ቢሆንም ወሬው የተሰማው ትናንት ማምሻውን እንደሆነ ABC ኒውስ ፅፏል፡፡
200 ያህል ሰዎችን ከአደጋው ማትረፍ እንደተቻለ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ብዛታቸው ይሄን ያህል ነው ባይባልም የገቡበት የጠፋም አሉ ተብሏል፡፡
በአካባቢው የቅዳሜ እለቱ የጀልባ ተገልብጦ መስጠም አደጋ በሳምንት ጊዜ 2ኛው እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ኮንጎ ኪንሻሣ የጀልባ አደጋ የሚደጋገምባት እንደሆነች ዘገባው አስታውሷል፡፡
የፈረንሳይዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤልሳቤት ቦረን በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ኤልሳቤት ቦረን በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡት በዚያ ችግር ለጠናባቸው ፍስጤማውያን ሲቪሎች ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ እንዲያመች እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡
ሐማስ ከ2 ሳምንታት በፊት ወደ እስራኤል በመዝለቅ ድንገት ደራሽ ጥቃት በማድረስ ከ1 ሺህ 400 ያላነሱ ሰዎችን መግደሉ እስራኤልን አራስ ነብር አድርጓል፡፡
በጋዛ ሰርጥም እጅግ መጠነ ሰፊ የአየር እና የከባድ መሳሪያዎች ድብደባ እየፈፀመች ነው፡፡
በጋዛ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት ፍልስጤማውያን ብዛት ከ5 ሺህ ተሻግሯል፡፡
ከእለት እለትም በሰርጡ ሰብአዊ ቀውስ እየገዘፈ መምጣቱ ይነገራል፡፡
በአሜሪካ ተረኛ ያልሆነበትን የመንገደኞች አውሮፕላን ከአየር ላይ ለመከስከስ ሞክሯል የተባለ አብራሪ ክስ እንደተመሰረተበት ተሰማ፡፡
አውሮፕላኑ የመከስከስ አደጋ የተጋረጠበት ከዋሽንግተን ወደ ሳን ፍራንሲስኮ በማምራት ላይ በነበረበት ወቅት እንደሆነ ABC ኒውስ ፅፏል፡፡
ተራው ያልሆነው ፓይለት ወደ አብራሪዎቹ ክፍል በመዝለቅ የአውሮፕላኑን ሞተሮች የማጥፋት ሙከራ አድርጎ ነበር ተብሏል፡፡
ተረኛው አብራሪ እና ረዳቱ ተረባርበው የግለሰቡን አውሮፕላን ሆን ብሎ የመከስከስ ሙከራ እንዳከሸፉበት በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
በግብግቡ ወቅት አውሮፕላኑ በአጣዳፊ ሁኔታ በፖርት ላንድ ለማረፍ መገደዱ ታውቋል፡፡
ግለሰቡ በዚያ በፀጥታ ሀይሎች ተይዞ መታሰሩ ተሰምቷል፡፡
ሆን ተብሎ የመከስከስ አደጋ ተጋርጦበት የነበረው የመንገደኞች አውሮፕላን 80 ሰዎችን አሳፍሮ እንደነበር ዘገባው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments