top of page

ጥቅምት 18፣2017 – የባህር ማዶ ወሬዎች


የሩሲያ ጦር በምስራቃዊ ዩክሬይን ወደፊት እየገፋ ነው ተባለ፡፡


ጦሩ ኢስማየልቭካ የተባለውን አካባቢ መያዙን ቲአርቲ ዎርልድ(TRT World) ፅፏል፡፡


ኩራኪቭካ የተባለችውን ከተማ ከዩክሬይን ጦር ለመንጠቅ እየከበባት ነው ተብሏል፡፡


ባለፉት ጥቂት ወራት በምስራቃዊ ዩክሬይን የሩሲያ ጦር በርካታ ስፍራዎችን በእጁ ማስገባቱ ይነገራል፡፡


የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባዊያን ለዩክሬይን በሚያስታጥቋት መሳሪያዎች ግዛት ተሻጋሪ ጥቃት ካደረሰችብን ለአጠቃላይ ምላሹ እየተዘጋጀንበት ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


ፑቲን የምንለውን ምዕራባዊያን በደንብ ይረዳታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉ መናገራቸው ተጠቅሷል፡፡


የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አርጋቺ በቅዳሜው ጥቃት አሜሪካም የእስራኤል አጋዥ ነበረች አሉ፡፡


አባስ አርጋቺ አሜሪካም የጥቃቱ ግልፅ ተካፋይ ነበረች ማለታቸውን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡


ቀደም ሲል እስራኤል በኢራን ላይ የአየር ጥቃቱን የፈፀምኩት ብቻዬን ነው ብላ ነበር፡፡


የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር /ፔንታገን/ ሹሞች በጥቃቱ እኛ የለንበትም ለማለት አላረፈዱም፡፡


የኢራን ሹሞች የእስራኤል የአየር ጥቃት ስላደረሰባቸው ጉዳት በዝርዝር ባይናገሩም 4 ወታደሮቻችን ተገድለውብናል ብለዋል፡፡


ከወር ገደማ በፊት ኢራን በእስራኤል ላይ በ180 ሚሳየሎች ጥቃት እንደሰነዘረች ሲነገር መቆየቱን መረጃው አስታውሷል፡፡



ጋና ለቡርኪናፋሶ አማጺያን በአቅርቦት ማዕከልነት እያገለገለች ነው መባሉን የአገሪቱ ሹሞች አስተባበሉ፡፡


ሬውተርስ በስም ያልተጠቀሱ የጋና የደህንነት ሹሞችን ጭምር አነጋግሬ የቡርኪናፋሶ አማጺን ጋናን በስንቅ እና ትጥቅ አቅርቦት ማዕከልነት እየተገለገሉ መሆኑን ደርሼበታለሁ የሚል ዘገባ መስራቱን TRT አፍሪካ ፅፏል፡፡


የጋና መንግስት ግን በይፋዊ መግለጫው ከቡርኪናዎቹ አማጺያን ጋር አንዳችም ጉዳይ የለንም ፤ እንዲህ ዓይነቱንም ጣልቃ ገብነት አንደግፍም ብሏል፡፡


ቡርኪናፋሶ በተለያዩ አማጺ ቡድኖች ቁም ስቅሏን ስታይ ከ10 ዓመታት በላይ ሆኗታል፡፡


ጋና ከቡርኪናፋሶ ጋር 600 ኪሎ ሜትር ድንበር እንደምትጋራ መረጃው አስታውሷል፡፡



የሊባኖሱ የጦር ድርጅት(ሔዝቦላህ) የሰሜናዊ እስራኤል 25 መንደሮች ነዋሪዎች ለቅው እንዲወጡ አስጠነቀቀ፡፡


ቀደም ሲል እስራኤል የወሰን አካባቢ የደቡብ ሊባኖስ ነዋሪዎች ለቅቀው እንዲወጡ በሰጠችው ማስጠንቀቂያ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩት መፈናቀላቸውን ሚድል ኢስት ሞኒተር አስታውሷል፡፡


ከሊባኖሷ ርዕሰ ከተማ ቤይሩት ደቡባዊ ክፍልም ብዙዎቹ ለቅቀው መውጣታቸው ተጠቅሷል፡፡


አሁን በተራው ሔዝቦላህም የሰሜናዊ እስራኤል መንደሮች ነዋሪዎች በአፋጣኝ ከመኖሪያቸው ለቅቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቁ ተሰምቷል፡፡


የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ የየብስ ዘመቻውን ከጀመረ ቆይቷል፡፡


በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችም የአየር ድብደባ እየፈፀመ ነው፡፡



የጆርጂያው የምርጫ ውጤት በከባዱ እያወዛገበ ነው ተባለ፡፡


የቅድሚያ ውጤቱ ገዢው የጆርጂያ ድሪም የፖለቲካ ማህበር ማሸነፉን እንደሚጠቁም ቢቢሲ ፅፏል፡፡


4 ተቃዋሚ የፖለቲካ ማህበሮች ድምፃችንን ተሰርቀናል ፤ ተጭበርብረናል የሚል ክሳቸውን አጉልተው እያሰሙ ነው፡፡


ተቃዋሚዎቹ አገሪቱን የአውሮፓ ህብረት አባል የማድረግ ፍላጎት ያላቸው ናቸው ተብሏል፡፡


ጆርጂያ ከቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት 15 አባል ሪፖብሊኮች አንዷ ነበረች፡፡


የአገሪቱ ምርጫ አከናዋኝ መስሪያ ቤት በተቃዋሚዎች ለመንግስት ያደላላል በሚል እየተነቀፈ ነው፡፡


ከወዲሁ የምርጫው ውጤት ማራበሽ ጀምሯል ተብሏል፡፡



የቦሊቪያው የቀድሞ ፕሬዘዳንት ኢቮ ሞራሌሽ በመኪና እየተጓዝኩ ሳለ የግድያ ሙከራ ተደረገብኝ አሉ፡፡


ሞራሌስ ተቃጥቶብኛል ያሉትን የግድያ ሙከራ አምርረው ማውገዛቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የግድያ ሙከራው ሲደረግብኝ በጥይት ተበስቷል ያሉትን የመኪናቸውን የፊት መስታወት ሽንቁር በየማህበራዊ ድረ ገጹ እዩልኝ ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡


ኢቮ ሞራሌስ የፖለቲካ ማህበር ለዚህ የግድያ ሙከራ የፕሬዘዳንት ሉዊስ አርሴ መንግስት ተጠያቂ ነው ማለቱ ተሰምቷል፡፡


ፕሬዘዳንቱ በበኩላቸው እንዲህ ዓይነቱ የአመፅ ድርጊት በጭራሽ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡


ጉዳዩ በዝርዝር እንደሚመረመርም ቃል መግባታቸው ተሰምቷል፡፡


ሞራሌስ አሁንም በምህፃሩ ማስ የተሰኘውን ግራ ክንፈኛ የፖለቲካ ማህበር እየመሩ መሆኑን መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ

コメント


bottom of page