አቢሲንያ ባንክ ''የሀገር ውስጥ ቁጠባን እና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማበረታታት'' በሚል አዘጋጀሁት ላለው ሽልማት ባለዕድለኞችን በዕጣ ለየ።
ባንኩ ''እንሸልምዎ'' በማለት የሰየመው ይህ ሽልማት ሲያካሄድ ለ6ተኛ ጊዜው ነው ተብሏል።
እድለኞች የተለዩበት የእጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አዳራሽ ተከናውኗል።
በባንክ ኢንደስትሪ በየጊዜው ተለዋዋጭ የሆነውን የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት በቴክኖሎጂ እና በሰለጠነ የሰው ኃይል በመታገዝ የተቀላጠፈ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ የተለያዩ የማበረታቻ ሽልማቶችን በማዘጋጀት ደንበኞችን መሸለም የተለመደ አሠራር እየሆነ እንደመጣ ባንኩ ተናግሯል፡፡
ይህ አሠራር የሀብት ማሰባሰብ ሥራዎችን በማሳደግ ኢንዱስትሪ፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ከፍ ለማድረግ በሚደረገው ሀገራዊ ርብርብ የራሱን አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብሎ እንደሚያምንም ባንኩ አስረድቷል።
በዛሬው የዕጣ ማውጣት መርሀ ግብር እድለኛ የሆኑ ቆጣቢዎች ዝርዝርም፤ በባንኩ የማህበራዊ የትስስር ገፆች ላይ እና በተለያዩ የመገናኛ መንገዶች እንደሚያሳውቅ አቢሲኒያ ባንክ ተናግሯል።
ባንኩ የደንበኞችን ቁጥር ለመጨመር፣ የሀገር ውስጥ ቁጠባ እና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ይኸንኑን እና ሌሎች መሰል የሀብት ማሰባሰብ ሥራዎችን የሚያሳድጉ የማበረታቻ አሠራሮችን በመንደፍ እቀጥልበታለሁ ሲል ተናግሯል።
ማንያዘዋል ጌታሁን/ወንድሙ ሀይሉ
Comments