የአሜሪካ የመከላከያ መስሪያ ቤት (ፔንታገን) ሰሜን ኮሪያ 10,000 ያህል ወታደሮቿን ወደ ሩሲያ መላኳን አረጋግጫለሁ አለ፡፡
ፔንታገን በቃል አቀባዩ አማካይነት የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ወደ ሩሲያ መላክ የዩክሬይኑን ጦርነት በእጅጉ ያባብሰዋል ማለቱን አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች እስካሁን ወደ ዩክሬይን ስለመዝለቃቸው የተሰማ ነገር የለም፡፡
ያም ሆኖ ወደ ሩሲያ ኩርስክ ግዛት ተልከዋል ተብሏል፡፡
የዩክሬይን ሰራዊት ከዋነኛው ጦር ግንባር ወደ ራቀው የደቡባዊ ሩሲያ ኩርስክ ግዛት ከዘለቀ ወራት አስቆጥሯል፡፡
የዩክሬይን ሰራዊት የሩሲያን ጦር ከዋነኛው የጦር ግንባር ወደ ኩርስክ ለመሳብ የዘየደው የጦር መላ እምብዛም እንዳልተሳካ ይነገራል፡፡
የእስራኤል ፓርላማ ለፍልስጤማውያን ሰብአዊ እርዳታ በማቅረብ የተሰማራውን የተባበሩት መንግስታት አካል(አንሩዋን) ተግባራት የሚሽመደምዱ ሁለት ሕጎችን አፀደቀ፡፡
አንደኛው ሕግ አንሩዋ በእስራኤል መሬት ማንኛውንም ተግባር እንዳያከናውን የሚከለክል መሆኑን ዘ ሒንዱ ፅፏል፡፡
ሌላኛው ሕግ ደግሞ እስራኤል ከአንሩዋ ጋር የነበራት ማንኛውም ግንኙነት እንዲቋረጥ የሚጠይቅ ነው ተብሏል፡፡
የህጉ መፅደቅ በተለይም በጋዛ ሰርጥ የሚታየውን ሰብአዊ ቀውስ ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚያደርገው ተሰግቷል፡፡
የረድኤት ድርጅቱ በገጠመው ፈተና ጉዳይ የእስራኤል አጋሮች የሆኑ አገሮች ሳይቀር ሀሳብ ገብቷቸዋል ተብሏል፡፡
እስራኤል አንሩዋ የፍልስጤማውያን ሰላማዊ ሰዎች ሳይሆን የሀማስ ረዳት ነው ስትል ፈርጃዋለች፡፡
የእስራኤል እርምጃ በጋዛ የሚገኙ 1.9 ሚሊዮን ፍልስጤማውያን ተፈናቃዮችን መከራ እና ስቃይ ይበልጥ እንደሚያከፋው መረጃው አስታውሷል፡፡
በቀይ ባህር ባብኤል ማንድብ ሰርጥ በማለፍ ላይ የነበረ መርከብ ጥቃት ተሰነዘረበት ተባለ፡፡
በመርከቡ አቅራቢያ ሁለት ፈንጂዎች እንደወደቁ ካፒቴኑ መናገራቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
ጥቃት የተሰነዘረበት መርከብ የየትኛው አገር እና የማንኛውም ኩባንያ እንደሆነ አልተጠቀሰም፡፡
በመርከቡ ላይ ለተሰነዘረው ጥቃት ፈጥኖ ሀላፊነቱን የወሰደ ወገን የለም ተብሏል፡፡
ከምናልባትም በላይ ጥቃት አድራሾች የየመን ሁቲዎች ሳይሆኑ እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡
ሁቲዎቹ በቀይ ባህር በሚተላለፉ የእስራኤል እና የአጋሮቿ መርከቦች ላይ ጥቃት በማድረሳችን እንገፋበታለን ካሉ አመት ሊሞላቸው እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በቅዳሜው የአየር ጥቃታችን የኢራንን የሚሳየል ማምረቻ ተቋማትን በእጅጉ አሽመድምደናል አሉ፡፡
ኔታንያሁ የአገራቸው አየር ሀይል በኢራን የፈፀመው የአየር ድብደባ እጅግ በጣም ከባድ ፣ ውጤታማ እና ዒላማውን የጠበቀ ነበር ማለታቸውን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡
ታላቅ ፋይዳ የነበረው ድብደባ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
ኢራን በድብደባው 4 ወታደሮች ብቻ ተገድለውብኛል ስትል ጥቃቱን አቃላው ነበር፡፡
ኋላ ላይ ግን የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላ ዓሊ ሐሚኒ የእስራኤልን ድብደባ ያን ያህል የምናጋንነውም ፣ ያን ያህል የምንቃልለውም አይደለም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ኢራን ለቅዳሜው የእስራኤል የአየር ጥቃት አፀፋዬ አይቀርም ማለቷ ተጠቅሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
Komentáře