ባለፉት 3 ወራት ከወጪ ንግድ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የተሳካው 1.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናግረዋል፡፡
ገቢው በዚህ ልክ ከቀጠል በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ከ5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ይገኛል ብለዋል፡፡
‘’በዚህ ዓመት ከቡና የወጪ ምርት ቢያንስ 2 ቢሊየን ዶላር ገቢ እንዲያመጣ እየተሰራ ነው’’ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘’ባለፉት 3 ወራት ከቡና ውጪ ንግድ ከ5 መቶ ሚልየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል’’ ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ባለፉት 3 ወራት የውጪ ኢንቨስትመንት በ6.4 በመቶ አድጓል አሁንም ወደ ዘርፉ ለሚገቡ ሰዎች አሰራሮችን ቀላል ማድረግ አለብን ብለዋል፡፡
‘’እንደ ሀገር የውጪ ባለሀብቶች ለመሳብ በሚል ፋይናንስ ተቋማት አከባቢ የነበሩ ችግሮች እየተፈቱ ነው’’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ባላፉት ሶስት ወራት በተለያየ መንገድ ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ 3.4 ቢሊዮን ዶላር መጥቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጭማሪ ተመዝግቦበታል ብለዋል፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ሃብት 400 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡
በአጠቃላይ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው 27 ቢሊዮን ዶላር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ይጠበቃል ተብሏል፡፡
ከዚህ በፊት ፍራንኮ ቫሉታን ፈቅደን የነበረው ወደ ውጪ ሸሽቶ የነበረን ሃብት ለመመለስ ነበር ከዛም ባለፈ የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት እራሳቸው እስኪያደራጁ ለመጠበቅ ነበር አሁን ፍራንኮ ቫሉታ ላይ ማስተካከያ ይደርግበታል ብለዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት 3 ወራት 170 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ ምርት ምጣኔ ወይም ጂዲፒ አንፃር የምትሰበስበው ገቢ እጅግ አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመት ከፌደራል እና ከክልል መንግስት 1.5 ትሪሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ዋንኛ እቅዱ ሀገሪቱ ካላት አጠቃላይ ምርት አኳያ ከግብር የሚገኘው ገቢ ቢያንስ 8.5 ከመቶውን ለመሰብሰበው ነው ብለዋል፡፡
በረከት አካሉ
Comments