በኢትዮጵያ በባንኮች ገንዘብ ከሚያስቀምጡት አብዛኛዎቹ ወይም 95 በመቶ የሚሆኑት በባንክ ያለው የገንዘብ መጠን ከ100,000 ብር በታች ነው ተባለ።
ይህን የሰማነው ዛሬ የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ወደ ሥራ መግባቱን በተነገረበት ጊዜ ነው።
በተለያዩ ገንዘብ ተቋማት ላለ ተቀማጭ ገንዘብ ዋስትና የሚሰጥ የገንዘብ መድን ፈንድ ተቋቁሞ ዛሬ በይፋ ስራ ጀምሯል፡፡
ይህ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነው ተብሏል።
ከዛሬ ጀምሮ በየትኛውም የፋይናንስ ተቋም ገንዘብ ያስቀመጡ ሰዎች ገንዘባቸው በዚሁ ፈንድ ዋስትና ያገኛል የተባለ ሲሆን ጥበቃው የሚመለከተው 100,000 ብር እና ከዚያ በላይ የሆነን ብቻ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ መርጋ ዋቆያ ተናግረዋል።
ይህም በፋይናንስ ዘርፍ ላይ ከተፈፀሙ ለውጦች አንዱ ነው ተብሏል።
ፈንዱ አደረጃጀቱ ምን ይመስላል የሚለውን የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ አቶ ሰለሞን ደስታ ተናግረዋል።
የፈንዱ ስልጣንና ተግባር በክፍያ ካዝናነት የተገደበ ነው ተብሏል።
አላማው ህዝባዊ ነው የተባለ ሲሆን የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ ፈንድ በመንግስት ይተዳደራል ተብሏል።
ምክትል ገዢው አንድ የፋይናንስ ተቋም የሚወድቅ ከሆነ ኮሽታ ሳያሰማ ህዝቡን ሳይረብሽ ኢኮኖሚውንም ሳይረብሸው እንዲወጣ ፈንዱ ይሰራል ብለዋል።
ይህ በሚሆን ጊዜም በመድን የተሸፈነውን ገንዘብ ለአስቀማጩ ከ 7 ቀን እስከ 90 ቀን ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንደሚመለስ አስረድተዋል።
147 ሀገራት የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ተቋም አላቸው የተባለ ሲሆን ኢትዮጵያ 148ተኛ ሀገር ሆናለች።
ተህቦ ንጉሴ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments