top of page

ጥቅምት 25፣2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Nov 4, 2024
  • 1 min read

የየመን ሁቲዎች የአገሪቱን መንግስት ለማዳከም ከአልቃይዳ ፅንፈኛ ቡድን ጋር እየተባበሩ ነው ተባለ፡፡


ሁቲዎቹ ከአልቃይዳ ጋር እየተባበሩ መሆኑን ደርሼበታለሁ ያለው የተባበሩት መንግስታት የባለሙያዎች የክትትል ቡድን እንደሆነ አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡


የየመን ሁቲዎች ርዕሰ ከተማዋ ሰንዓን ጨምሮ አብዛኛውን የአገሪቱን ሰሜናዊ ክፍል ሲያስተዳድሩ ከ10 አመታት በላይ ሆኗቸዋል፡፡


አለም አቀፋዊ እውቅና ያለው የየመን መንግስት በአሁኑ ወቅት መቀመጫው በደቡባዊቱ የወደብ ከተማ ኤደን ነው፡፡

የየመን ሁቲዎች አለም አቀፋዊ እውቅና ያለውን የየመን መንግስት ለማዳከም ከአልቃይዳ ፅንፈኛ ቡድን ጋር እየተባበሩ ነው ተብሏል፡፡


ትብብሩ የሶማሊያውን ፅንፈኛ ቡድን አልሸባብን እንደሚጨምር ተጠቅሷል፡፡


ስለ ባለሙያዎቹ ግኝት ከሁቲዎቹ በኩል የተሰማ አስተያየት የለም፡፡


በዩጋንዳ በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ የወረደ መብረቅ 14 ሰዎችን ገደለ፡፡


በመብረቁ ሕይወታቸው ካለፈው ሌላ 34 ሰዎች ደግሞ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው TRT አፍሪካ ፅፏል፡፡


በአደጋው ሕይወታቸው ያለፈው በሙሉ ሕፃናት እንደሆኑ ሹሞች ተናግረዋል፡፡


መብረቅ ወድቆ ሰዎችን የገደለው እና አካላዊ ጉዳት ያደረሰው በአገሪቱ ሰሜናዊ ምዕራብ በሚገኘው ፓላቤክ የስደተኞች መጠለያ ነው፡፡


ፓላቤክ የስደተኞች መጠለያ ከ80 ሺህ በላይ ስደተኞች መኖሪያ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡


በመብረቁ የሞቱት ህፃናት በእግር ኳስ ጨዋታ እረፍት ላይ ነበሩ ተብሏል፡፡



ደቡብ ኮሪያ ፣ ጃፓን እና አሜሪካ ጣምራ የአየር ሀይል የጦር ልምምድ አደረጉ፡፡


የሶስቱ አገሮች ጣምራ የአየር ሀይል የጦር ልምምድ ከባድ ቦምብ ጣዮችም የተሰለፉበትም እንደሆነ አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡


የእነ ደቡብ ኮሪያ ጣምራ የአየር ሀይል ጦር ልምምድ በቅርቡ ሰሜን ኮሪያ ታላቅ የባልስቲክ ሚሳየል ለሙከራ መተኮሷን የተከተለ ነው ተብሏል፡፡


ልምምዱ ሰሜን ኮሪያ ለሙከራ የተኮሰችው የባልስቲክ ሚሳየል መልስ እንደሆነ ተነግሯል፡፡


ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ ከ70 አመታት በፊት ታላቅ ጦርነት ካካሄዱ ወዲህ ልሳነ ምድሩ ውጥረት ተለይቶት አያውቅም፡፡


ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የጦር ፍጥጫው አይሏል፡፡


ቀደም ሲል ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ ጋር ወሰን አልባ የመከላከያ የትብብር ስምምነት መፈራረሟን መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page