ጥቅምት 26፣2017 - የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በ131 ሚሊዮን ብር ወጪ በቡና ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ድጋፍ አደረኩ አለ፡፡
- sheger1021fm
- Nov 5, 2024
- 1 min read
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በ131 ሚሊዮን ብር ወጪ በቡና ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ድጋፍ አደረኩ አለ፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለአርሶ አደሮቹ ድጋፍ አደረኩ ያለው ከዩኤንዲፒ (UNDP) ባገኘሁት 9 ሚሊዮን ዶላር ነው ብሏል፡፡
ከተገኘው ድጋፍ ላይም በመጀመሪያ ምዕራፍ 131 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለቡና ምርት የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን መግዛቱን ተናግሯል፡፡
በዚህም በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ እና ኦሮሚያ ክልልን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎለታል፡፡
የቡናን ዘርፍ በመንግስት ከሚገኝ ገንዘብ ብቻ ማሳደግ እንደማይቻል የተናገሩት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ(ዶ/ር) ከሌሎች ተቋማት ድጋፎችን በማፈላለግ ስራዎችን እየከወንን ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደምም ከተለያዩ ተቋማት በተገኘ ድጋፍ ዘርፉን የማሳደግ ስራ ተሰርቷል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ ፤አሁንም ከ #UNDP የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ለዘርፉ ማደግ ትልቅ አስተዋፆኦ አለው ብለዋል፡፡

የሚመረቱ ቡናዎች ጥራታቸው የተጠበቀ እንዲሆን እና ምርትን ለማሳደግ ይረዳሉ የተባሉ የተለያዩ ማሽኖች ለክልሎቹ ተሰጥቷል፡፡
ያረጁ የቡና ዝርያዎችን በአዳዲስ መተካት እና መጎንደል የሚያስችሉ ማሽኖችን ግዥ ተከናውኖ ለአርሶ አደሮች መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ከ UNDP የተገኘው አጠቃላይ ድጋፍም 440,000 የሚሆኑ አነስተኛ የቡና አልሚዎች እንደሚደግፍ የተናገሩት በፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ወርቁ ፕሮጀክቱ ከአራቱም ክልሎች 22 ወረዳዎችን ተደራሽ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከ UNDP ባገኘው ድጋፍ በአራቱም ክልል 22 ወረዳዎች ላይ ስራዎችን የሚሰራ እንደሆነ የተናገረ ሲሆን የሰባት ዓመት እድሜ ያለው ፕሮጀክት ነው ተብሎለታል፡፡
ፋሲካ ሙሉወርቅ
Comments