አሁን ያሉት ተደራራቢ ችግሮች በዚህ ከቀጠሉ ከ5 ዓመት በኋላ ረሃብን ከአለም ለማጥፋት የተቀመጠው ግብ እንደማይሳካ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተናግሯል፡፡
ተመድ ዘላቂ የልማት ግቦች ብሎ ካስቀመጣቸው አጀንዳዎች መካከል በ2030 ረሃብን ከዓለም ማጥፋት አንዱ ነው፡፡
ይሁንና በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት ረሃብ ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ መጥቷል፡፡
በኢትዮጵያ ከ8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አፋጣኝ የምግብ ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡
በአለም ዙሪያም ከ800 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል ያለው ድርጅቱ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የቀሩት 5 ዓመታት ብቻ በመሆናቸው አለም በረሃብ ያለችበትን ደረጃ መለስ ብሎ መቃኘት እንዳስፈለገ ተናግሯል፡፡
ለዚህም እንዲረዳ ከረሃብ ነፃ አለምን መፍጠር ይቻላል ወይ? በሚል ለ3 ቀናት የሚዘልቅ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማህማት፣ ከተለያዩ ሃገራት የተወከሉ እንግዶች በተገኙበት በአድዋ ሙዚየም ተጀምሯል፡፡
በጉባኤው ረሃብን በመቀነስ ረገድ አለም ያለችበትን ደረጃ በተመለከተ የተጠናው ጥናት የሚቀርብበት፤ ላይሳካ ይችላል የተባለው ረሃብን የማትፋት ስራ ምን እንቅፋቶች ነበሩት በሚለውና ወደፊት ምን ዓይነት መንገድ እንከተል በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመከርበት በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(UNIDO)በኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ አቶ አሰግድ አዳነ ለሸገር ራዲዮ ተናግረዋል፡፡
በአለም ዙሪያ ተባብሶ ለቀጠለው ረሃብ ዋነናው ምክንያት የምርታማነት ማነስ እና የስራ እድል አለመኖር መሆኑ በጉባኤው ተነስቷል፡፡
አፍሪካ ግብርናዋን አለማዘመኗ እንዲሁም ያላትን ወጣት ሃይል በሚገባ አለመጠቀሟ ድህነት ቅነሳ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዳታመጣ ምክንያት መሆኑም ተነስቷል፡፡
ለ3 ቀናት በሚቀጥለው ምክክር በአጀንዳ 2030 የተሻለ ተሞክሮ አላቸው የተባሉ ሃገራት ተሞክሯቸውን የሚያቀርቡበት፣የሚያሰራ ፖሊሲ ያላቸው፣ ግብርናቸውን ያዘመኑ ሃገራት ተሚክሯቸውን የሚያቀርቡበትም ይሆናል ተብሏል፡፡
በጉባኤው መክፈቻ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፉት 6 ዓመታት የግብርናው ምርት በእጥፍ አድጓል፤የሚታረስ መሬት መጠንም በእጥፍ አድጓል ብለዋል፡፡
የግብርና ምርቶችን እሴት ጨምሮ ማቀነባበር ላይም ተስፋ ሰጪ ጅምሮች እንዳሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ጠቅሰዋል፡፡
አቶ አሰግድም ኢትዮጵያ በምግብ እራስን ለመቻል የጀመረችው ስራ በጥሩ ተሞክሮነት እንደሚቀርብ ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም ይህ ግብ እንዳይሳካ እንቅፋት ከሆኑ ችግሮች መካከል ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹን የአፍሪካ ሃገራት እየፈተነ ያለው የሰላም እጦት መሆኑን አንስተዋል፡፡
በጉባኤው እነዚህና ሌሎችም ከ5 ዓመት በኋላ ረሃብን ከአለም ለማጥፋት እንቅፋት ሆነዋል የተባሉ ችግሮች ተለይተው ምን ቢደረግ ይሻላል የሚለውን ለመወሰን ግብአት የሚሰበሰብበት እንደሆነም ሰምተናል፡፡
ምንታምር ፀጋው
Comments