ስምምነቱ በመጋዘን ደረሰኝ የብድር አገልግሎት ጋር በተገናኘ መሆኑ ተነግሯል ።
በስምምነቱ መሰረት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ መጋዘኖች ደረጃ ተሰጥቷቸው በተለያዩ አካላት የሚከማቹ የግብርና ምርቶችን እንደማስያዣነት በመጠቀም የምርቶቹ ባለቤቶች ከአማራ ባንክ ቀልጣፋ የብድር አገልግሎት ማግኘች የሚያስችላቸው መሆኑ ተነግሯል።
የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት አንድ አምራች ወይም ተገበያይ ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ መጋዘን ምርቱን በማስገባትና የሚቀበለውን የመረከቢያ ደረሰኝ እንደ ማስያዣ በመጠቀም ከምርት ገበያው ጋር ውለታ ካሰሩ ባንኮች የአጭር ጊዜ ብድር የሚያገኝበት የአሰራር ስርዓት መሆኑን በፊርማ ስነስርዓቱ ወቅት ሲነገር ሰምተናል።
የአማራ ባንክ እና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ስምምነት የግብርና ምርቶች በጊዜ ሳይወሰኑ ትክክለኛ ዋጋ እንዲያወጡ ያስችላል ሲሉ የምርት ገበያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ወንድምአገኝ ነገራ ተናግረዋል ።
የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት ገበሬው ወይንም ነጋዴው ዋጋ እስኪስተካከል ደረስ ምርቶችን በመጋዘን ይዞ እንዲቆይ እና ገበያው ላይ እጥረት እንዲፈጠር አያስችልም ወይ ተብለው የተጠየቁት የምርት ገበያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ወንድምአገኝ ነገራ የምርት ማከማቸት አይፈጠርም፣ የብድር ስምምነቱ ለአጭር ጊዜ በመሆኑ ገበያውም አይቸገርም ብለዋል።
አማራ ባንክ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር ያሰረው ስምምነት ገበሬውን፣ የህብረት ስራ ማህበራትን የፋይናንስ መሠረት ለማጠናከር፣ የኢኮኖሚ ዕድገትንና መረጋጋትን ለማስፈን፣ የፋይናንሻል አካታችነትን ለማጎልበት እና የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ ልማትን ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሄኖክ ከበደ ተናግረዋል ፡፡
አማራ ባንክ በአሁኑ ሰዓት ከ288 በላይ ቅርንጫፎች፣ ከ1.2 ሚሊየን በላይ ደንበኞች እንዲሁም ከ5,000 በላይ ሰራተኞ አሉኝ ብሏል።
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments