top of page

ጥቅምት 4፣2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች


በሊባኖስ ደቡባዊ ክፍል ተሰማርቶ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ሀይል (UNIFIL) የእስራኤል ጦር ወደ ጠቅላይ መምሪያዬ ጥሶ የመግባት ሙከራ አድርጓል ሲል ከሰሰ፡፡


ሰላም አስከባሪው ሁለት የእስራኤል ጦር ታንኮች በራሚያህ የሚገኘውን የጠቅላይ መምሪያዬን ዋና መግቢያ ደርምሰውታል ማለቱን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በሰላም አስከባሪዎቹ ላይ የሚፈፀም ማንኛውም ጥቃት በጦር ወንጀል ያስጠይቃል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


የእስራኤል የጦር ሹሞች ቀደም ሲል ከአቅራቢያው በሔዝቦላህ ሮኬት ተተኩሶብናል የሚል መሟገቻ እያቀረቡ ነው ተብሏል፡፡


የራሚያሁ አጋጣሚ በእስራኤል ጦር እና በሰላም አስከባሪው ሀይል መካከል ነገሮች እየተካረሩ መምጣታቸውን እንደሚያሳይ መረጃው አስታውሷል፡፡




የሱዳን ጦር ጠቅላይ አዛዥ እና የመንግስቱ መሪ ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን የሱዳን መንግስት ጦር መልሶ በእጁ ያስገባትን የጃባል ሞያን ከተማ ጎበኙ፡፡


ጃባል ሞያ ከካርቱም በስተደቡብ ምስራቅ በ280 ኪሎ ሜትር የምትርቅና በሲናር ግዛት የምትገኝ ከተማ ነች፡፡


አልቡርሃን ጃባል ሞያን ትናንት የጎበኙት ጦራቸው ከተማይቱን ከRSF ካስለቀቃት ከጥቂት ቀናት በኋላ እንደሆነ ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡


የአል ቡርሃን ጉብኝት የጦራቸውን የውጊያ መንፈስ ይበልጥ ለማነቃቃት የታለመ ነው ተብሏል፡፡


በሌላ መረጃ የሱዳን መንግስት የጦር ጄት በደቡባዊ የካርቱም ክፍል በሚገኝ የገበያ ስፍራ በፈፀመው ድብደባ 23 ገበያተኞች መገደላቸውን የፃፈው ደግሞ ቢቢሲ ነው፡፡


የሱዳን መንግስት ጦር የገበያ ስፍራውን በጦር ጄት የመታው በአቅራቢያው የሚገኘውን የRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ጦር ሰፈር ዒላማ አድርጎ በፈፀመው ድብደባ ነው መባሉ ተሰምቷል፡፡



የቻይና ጦር በታይዋን ዙሪያ ገባ ታላቅ የተባለ የጦር ልምምድ ጀመረ፡፡


የቻይና የጦር ልምምድ ታይዋን ነፃነት አውጃለሁ ብላ እንዳትነሳ ለማስጠንቀቅ የታለመ ነው መባሉን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ታይዋን ራሴን የቻልኩ ነፃ አገር ነኝ ብትልም ቻይና ግን ታይዋንን እንዳፈነገጠች ግዛቷ እንደምትቆጥራት መረጃው አስታውሷል፡፡


ቻይና በታይዋን ዙሪያ ገባ ወደ ታላቅ የጦር ልምምድ የገባችው የነፃነት አቀንቃኝ ናቸው የሚሉት አዲሱ የታይዋን ፕሬዘዳንት ዊሊያም ላይ በቅርቡ የነፃነትን ጉዳይ በተመለከተ ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡


ቤጂንግ በታይዋን ዙሪያ ተደጋጋሚ ታላላቅ የጦር ልምምዶችን ማድረጓ በመረጃው ለትውስታ ተጠቅሷል፡፡


አዲሱን የቻይና ልምምድ መጀመር ተከትሎ ታይዋንም የጦር ተጠንቀቅ ደረጃዋን ከፍ አድርጋዋለች ተብሏል፡፡


በብራዚል የደረሰ የአውሎ ነፋስ አደጋ በጥቂቱ 7 ሰዎችን ገደለ ተባለ፡፡


የሳኦ ፓውሎ ግዛት የአደጋው ዋነኛው ሰለባ እንደሆነች አውት ሉክ ኢንዲያ ፅፏል፡፡


አውሎ ነፋሱ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ምንቅርቅራቸውን በማውጣቱ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቤቶችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሳትቷቸዋል ተብሏል፡፡


በርካታ ኤርፖርቶችም ተዘግተው እንደነበር በመረጃው ተጠቅሷል፡፡


የውሃ አቅርቦቱንም ማስተጓጎሉ ታውቋል፡፡


ዛፎችን እና የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ማማዎችን ገነዳድሶ ጥሏል፡፡


አውሎ ነፋሱ በሰዓት 108 ኪሎ ሜትር በሆነ ፍጥነት ሲምዘገዘግ እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡



የሊባኖሱ የጦር ድርጅት ሔዝቦላህ በእስራኤል ሰሜናዊ ክፍል በሰው አልባ በራሪ አካላት (ድሮኖች) በፈፀመው ጥቃት አራት ወታደሮች ሲገደሉ ከ60 በላይ የሚሆኑት ደግሞ አካላዊ ጉዳት ገጠማቸው ተባለ፡፡


አልጀዚራ እንደፃፈው የሄዝቦላህ የድሮን ጥቃት ከሐይፋ በስተደቡብ በሚገኘው የቤኒያሚኒያ የጦር ማሰልጠኛ ላይ ያጣጠረ ነበር ተብሏል፡፡


በውጤቱም 4 ወታደሮች ሲገደሉ ከ60 በላይ የሚሆኑት መቁሰላቸውን የእስራኤል የጦር ሹሞች ተናግረዋል፡፡


ሔዝቦላህም ለጥቃቱ ሀላፊነቱን እወስዳለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡


አካላዊ ጉዳት ከገጠማቸው የእስራኤል ወታደሮች መካከል ሰባቱ ለሕይወታቸው ያሰጋቸዋል ተብሏል፡፡


ሔዝቦላህ የድሮን ጥቃቱን የፈፀመው እስራኤል በሊባኖስ ላይ ለምታደርሰው የጦር ጥፋት አፀፋ ነው ብሏል፡፡


የኔነህ ከበደ

Comments


bottom of page