የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በሊባኖስ ደቡባዊ ክፍል ተሰማርቶ የሚገኘው የድርጅቱ ሰላም አስከባሪ ሀይል ተልዕኮ ያለ አንዳች መታወክ መቀጠል አለበት አለ፡፡
በቅርቡ ሰላም አስከባሪው ከእስራኤል ጦር በኩል ተደጋጋሚ ጥቃት እንደተሰነዘረበት አልጀዚራ አስታውሷል፡፡
የእስራኤል ጦር በሰላም አስከባሪው የጥበቃ ስፍራ ባደረሰው ጥቃት 5 ሰላም አስከባሪ ወታደሮች አካላዊ ጉዳት አጋጥሟችዋል ተብሏል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በደቡባዊ ሊባኖስ ሰፍሮ የሚገኘው ሰላም አስባሪ ሀይል ያለ አንዳች መዘግየት ከአካባቢው ለቅቆ እንዲወጣ የጠየቁት ሰሞኑን ነው፡፡
ምክር ቤቱ በስም ለይቶ ባይጠቅስም በደፈናው ሁሉም ባለድርሻ ወገኖች የሰላም አስከባሪውን ደህንነት ሊያከብሩ ይገባል የሚል መግለጫ አውጥቷል፡፡
እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ የየብስ ዘመቻዋን ከጀመረች መሰንበቷን መረጃው አስታውሷል፡፡
በኬንያ ኤም ፖክስ (M pox) በተሰኘው የዝንጀሮዎች ፈንጣጣ ከተያዙት መካከል የአንዱ ሕይወት አለፈ ተባለ፡፡
በኬንያ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ብዛት 13 መድረሱን ዘ ኢስት አፍሪካን ፅፏል፡፡
በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ቅርበት የነበራቸውን የመከታተሉ ተግባር መቀጠሉ ታውቋል፡፡
ኮንጎ ኪንሻሣ የወረርሽኙ ተፅዕኖ በእጅጉ የበረታባት አገር ነች፡፡
ኤም ፖክስ በአፍሪካ በ10 ሀገሮች ተከስቶ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡
የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ መስሪያ ቤት አፍሪካ CDC ኤም ፖክስን አህጉራዊ የጤና ስጋት ነው ሲል ካወጀ ቆይቷል፡፡
የየመን ሁቲዎች በቀይ ባህር ተላላፊ መርከቦች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ግብፅን ኪሳራ ላይ እየጣላት ነው ተባለ፡፡
ሁቲዎቹ እስራኤል የጋዛ የጦር ዘመቻዋን እንድታቆም ለማስገደድ በሚል በቀይ ባህር በሚተላለፉ የአጋሮቿ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ቀጥለዋል፡፡
ይህም ግብፅ በስዊዝ ቦይ በኩል ከሚተላለፉ መርከቦች የምታገኘውን ገቢ ከብዙ እንዳስቀረባት ታውቋል፡፡
የአረብ ሊግ ዋና ፀሐፊ አህመድ አቡል ጋየት እንደተናገሩት ግብፅ በሁቲዎቹ ጥቃት ምክንያት የ6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አጥታለች፡፡
ሁቲዎቹ ሰንዓን ጨምሮ አብዛኛው የየመንን ሰሜን ክፍል ያስተዳድራሉ፡፡
የኢራንም ሁነኛ የጦር እና የፖለቲካ ሸሪኮች መሆናቸው ይነገራል፡፡
የኔነህ ከበደ
Comments