ጥቅምት 6፣2017 - ከሰሞኑ በአዲስ አበባና አካባቢዋ እየጣለ ያለው ዝናብ ወቅቱን ያልጠበቀና ጉዳትም ሊያስከትል እንደሚችል የ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ተናገረ
- sheger1021fm
- Oct 16, 2024
- 1 min read
ከሰሞኑ በአዲስ አበባና አካባቢዋ እየጣለ ያለው ዝናብ ወቅቱን ያልጠበቀና ጉዳትም ሊያስከትል እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ተናገረ፡፡
በኢንስቲትዩቱ የትንቢያና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ(ዶ/ር) ከሰሞኑ እየጣለ ያለው ዝናብ ያልተለመደ መሆኑንና በተለይም በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ባለፈው ነሐሴ 2016 ዓ.ም በበጋ ወቅት የሚኖረውን ትንቢያ በሰጠበት ወቅት በተለይም አዲስ አበባን ጨምሮ በትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል ክልሎችና በመካከለኛውና በምስራቅ ኦሮሚያ ትንቢያ ሰጥቶ እንደነበር ያስታወሱት ባለሙያው ከሰሞኑ የተከሰተውም ይኸው ነው ብለዋል፡፡
ባለፈው ክረምት እነደነበረው አይነት ጎርፍ የማስከተል አቅም አይኖረው የተባለው ዝናብ መሰብሰብ ያለባቸውን የደረሱ ሰብሎችን ካገኘ ሊያበላሽ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
ወቅቱን የጠበቀ አይደለም፣ ተፅእኖውም ከክረምት የቀጠለ ነው የተባለው ዝናብ ምክንያቱ የላኒኖ ተፅዕኖ ነው ይላሉ፡፡
የአየር ትንቢያ መረጃዎቹ እንደሚያሳዩት የዝናቡ ስርጭት በሚቀጥሉት 10 ቀናትም ይቀጥላል፤ በተለይ የደረሱ ሰብሎች ያሏችሁ ጠንቀቅ በሉ ተብላችዋል፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ በተጠቀሱት አካባቢዎች የዝናብ ሥርጭቱ ይቀጥላል መባሉን ከሀላፊው ሰምተናል፡፡
ሙሉ ዘገባውን በድምፅ ለማድመጥ ይህንን ማስፈንጠሪያን ይጫኑ... https://tinyurl.com/yhmjyvvy
ምንታምር ፀጋው
Comments